የአፋር ታለንት አካዳሚ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎቹን ለመቀበል የመግቢያ ፈተና ሊሰጥ ነው::

የአፋር ታለንት አካዳሚ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎቹን ለመቀበል የመግቢያ ፈተና ሊሰጥ ነው::

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ፡ ታህሳስ 03/2016 ዓ.ም

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ እና የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ባደረጉት ስምምነት የተመሰረተው የአፋርታለንት አካዳሚ የመጀመሪያ ዙር ተማሪዎቹን ለመቀበል ዝግጅቱን አጠናቆ የመግቢያ ፈተና ሊሰጥ መሆኑ ተገልጿል::

የመግቢያ ፈተናውን ለመውሰድ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ የ8ተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ያስፈተኑ ትምህርት ቤቶች 900 የሚሆኑ ተማሪዎች እንደተመዘገቡ የተገለጸ ሲሆን: አካደሚው በ2016 ዓ.ም ማጣሪያውን የሚያልፉትን 100 ተማሪዎች የሚቀበል ይሆናል::

የመግቢያ ፈተናው የሚሰጥባቸው የትምህርት ዓይነቶች አፋርኛ ቋንቋ ፣ እንግሊዝኛ: ሒሳብ እና አጠቃላይ ሳይንስ መሆናቸው ተጠቁሟል።

ፈተናው ታህሳስ 6 እና 7 በአምስቱም ዞኖች በተዘጋጁ የፈተና ማዕከላት እንደሚሰጥ እና ሁሉም ማዕከላት የፈተና አስፈፃሚ አደረጃጀት እንደተዋቀረላቸው ተገልጿል፡፡

 

በአደረጃጀቱ መሰረት ለተመደቡት የፈተና አስፈፃሚዎች ማለትም ለዞን ማእከል አስባባሪዎች፣ ፈታኝ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮች እና የጸጥታ አካላት ተግባርና ኀላፊነታቸውን እና አጠቃላይ የፈተና አፈጻጸም ዙሪያ ገለፃ የተሰጠ ሲሆን ፈተናውን በታማኝነትና በቅንነት በመስጠት አካዳሚው የታቀደለትን አላማ እንዲያሳካ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ አደራ ተብሏል፡፡

ከሁለቱም ተቋማት የተዋቀረ የአካዳሚው የቴክኒክ ኮሚቴ ላለፉት ሁለት ወራት ተማሪዎችን ለመቀበል የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን ሲሰራ እንደቆየ እና በተለያዩ ክልሎች ያሉ በብሄራዊ ፈተና በማሳለፍ ጥሩ ተሞክሮ ካላቸው አዳሪ ትምረህርት ቤቶች ልምድ እንደተወሰደ ተነግሯል፡፡

አካዳሚው በየዓመቱ በ8ኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ከፍተኛ ውጤት የሚያመጡና በአካዳሚው የሚዘጋጀውን መግቢያ ፈተና የሚያልፉ ተማሪዎችን እንደሚያስተምር ተመላክቷል።

የአፋር ታለንት አካዳሚ ዓላማ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ከፍተኛ ተሰጥኦ ያላቸው: በስነ-ምግባራቸው የላቁ : በትምህርታቸው በሀገር እና በአለም አቀፍ መድረኮች ተወዳዳሪ: ቤተሰብን ብሎም ሀገርን የሚያኮሩ ተማሪዎችን ማፍራት ሲሆን: የዚህ ጥረት አካል የሆኑት የተማሪ ወላጆች ልጆቻቸውን በተመደቡበት የፈተና ማዕከል በማስፈተን ሂደቱን እንዲደግፉ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሀመድ ኡስማን ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትን ጨምሮ ከሰመራ ዩኒቨርሲቲ እና ከአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ የተውጣጡ አመራሮችና የአካዳሚው የቴክኒክ ኮሚቴ አባላት እና የፈተና አስፈፃሚዎች ተገኝተዋል::
===============
ህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈጻሚ
ማህበረሰቡን እናገለግላለን!!

Leave a Reply

Your email address will not be published.