የእውቅና እና የምስጋና ስነ-ስርዓት ተከናወነ።

የእውቅና እና የምስጋና ስነ-ስርዓት ተከናወነ።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ መስራች፣ ባለውለታ እና የቀድሞ ሰራተኛ የነበሩ ናቸው። በተለያየ አጋጣሚ አብረዋቸው የሰሩ ባለሙያዎች እና ባልደረቦቻቸው የፋይናንስ ሊቅ ናቸው ይሏቸዋል ፡፡ የገዘፈ የሂሳብ አሰራር እውቀትና ልምድ አላቸው፣ መረጃዎችን የመረዳት እና የመተንተን አቅማቸው ከፍ ያለ ነው። በአጠቃላይ በቆይታቸው በተቋሙ ውስጥ በታታሪ ሰራተኛነታቸው ይታወሳሉ፡፡

አቶ አንዋር ሸሂም ሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ 2005 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በዩኒቨርሲቲው የሰሩ ሲሆኑ፣ በቆዩባቸው አመታት የፋይናንስ ግዥና ንብረት አስተዳደር ስራን በዳይሬክተርነት መርተዋል፡፡

አቶ አንዋር የስራ ሰዓታቸውን ጠብቀው ቢሮ በመገኘት፣ ሰርተው በማሰራት ሰራተኞችን በማትጋት ይታወቃሉ፡፡ የዩኒቨርሲቲው የፋይናንስ ስራ በተሳለጠ ሁኔታ እንድሰራ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በስራቸው ለሚገኙ ሰራተኞቻቸው አመራር በመስጠት አስተምረዋል፡፡

ለዚህም ምስክር የሚሆነው፣ እስከ ዛሬ ድረስ ከርሳቸው ጋር የሰሩ ባለሙያዎች በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ስራን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

አቶ አኗር በአሁኑ ሰአት ኑሮአቸውን በስዊድን ሀገር ያደረጉ ሲሆን፣ ከበርካታ አመታት የውጭ ቆይታ በኋላ ወደ ቀድሞ ተቋማቸው በመምጣት በመጎብኘት ከህይወት ተሞክሯቸውና ልምዳቸው የቀሰሙትን እውቀት አካፍለዋል።

ሰመራ ዩኒቨርሲቲም እኒህን የተቋሙ መስራች እና ባለውለታ ሰራተኛ ለማመስገን እና እውቅና ለመስጠት የሽልማት ስነ-ስርዓት በዩኒቨርሲቲው ተከናውኗል፡፡

እንደነዚህ አይነት በተቋም ውስጥ ጠንካራ ሰራተኞችን ማመስገን እና እውቅና መስጠት ሰራተኞችን ከማበረታታት በተጨማሪ በታማኝነት ጠንክሮ በመስራት በታሪክ የማይረሳ አሻራን አስቀምጦ ማለፍም ጭምር በመሆኑ ለሌሎች ሰራተኞችም አርአያ እንድሆን ታስቦ የተዘጋጀ መድረክ ነው ሲሉ የሰመራ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት በስነ-ስርዓቱ ወቅት ገልፀዋል፡፡

*******

የህዝብና አለምአቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

ማህበረሰቡን እናገለግላለን!!