ዩኒቨርሲቲው ከወረቀት ነፃ (PAPERLESS/E-Exam) የማጠቃለያ ፈተና መስጠት ጀመረ።
==============
ሠመራ ዩኒቨርሲቲ:የካቲት 14/2016 ዓ.ም
ሠመራ ዩኒቨርሲቲ የ2016 ትምህርት ዘመን የአንደኛ ወሰነ-ትምህርት ከ1400 በላይ የ4ኛና 5ኛ አመት መደበኛ ተመራቂ ተማሪዎችን የማጠቃለያ ፈተና በዲጂታል መተግበሪያ (software) በመጠቀም ከወረቀት ነፃ (PAPERLESS) በሆነ መልኩ ፈተና መስጠት ጀምሯል።
ከወረቀት ነፃ ፈተና መስጠት ጠቀሜታው እንደሀገር በትኩረት እየተሰራበት ያለውን የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ፣ ቀጣይነት ያለው የዘመነ የፈተና ስርዓት ለመዘርጋት እና ተበታትኖ በተለያዩ ኮሌጆች ይሰጥ የነበረውን ፈተና ወጥ በሆነ ሁኔታ በአንድ ማእከል የወረቀትና ቀለም ወጪን የሚቀንስ አሰራር እንደሆነ የገለጹት በፈተናዎች ማዕከል የመውጫና ማጠቃለያ ፈተናዎች አስተባባሪ መ/ር ሀብታሙ ወንድምአገኘሁ ናቸው።
ከወረቀት ነፃ የማጠቃለያ ፈተናው ስርአተ-ትምህርቱን (Curriculum) መሰረት ያደረገና መምህራን ያስተማሩትን የትምህርት ይዘት የሚሸፍን የመመዘኛ ጥያቄ የሚያወጡበት አግባብ ስለተዘረጋ በኮርስ ደረጃ የተማሪዎችን ብቃት በትክክል ለመመዘን የሚያስችል ሲሆን ከወራት በኃላ ለሚወስዱት ሀገር አቀፍ የመውጫ ፈተና ተማሪዎች ያለባቸውን የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ችግር የሚፈታ፣ የፈተና መስጫ መተግበሪያውን አጠቃቀም የሚያስገነዝብ እንዲሁም የተማሪዎች የትምህርት አቀባበል የሚመዝንና ክፍተቶችን ለመገምገም የሚያስችል እንደሆነም አስተባባሪው ጠቁመዋል።
ዩኒቨርሲቲው መተግበሪያውን ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ጥቅም ላይ እንዲውል ያስቻለ ሲሆን በራሱ ባለሙያዎች አጠቃቀሙን, አስፈላጊነቱን, እና ማስተዳደሩን የሚያግዙ የአሰልጣኞች ስልጠና በወሰዱ መምህራን የሰጠ ሲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ግብረ-ሃይል አቋቁሞ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን መ/ር ሀብታሙ አንስተዋል።
ስራውን በበላይነት በመምራት የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ ፕሬዝዳንት, በማስተባበርና አጠቃላይ ስልጠናዎችን በመስጠት የፈተናዎች ማዕከል ዳይሬክቶሬት እንዲሁም የትምህርት ጥራት ሥራ አስፈፃሚ, ሁሉም ኮሌጆችና ትምህርት ቤቶች እንዲሁም መምህራን ወደ መተግበሪያው ቋት የሚገቡ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ እየሰሩ መሆኑም ተጠቅሷል።
በቴክኒክ ስራዎች በኩል የቤተ-ሙከራ ዳይሬክቶሬት፣ የአይሲቲ ሥራ አስፈፃሚ ፣ የጠቅላላ አገልግሎት ሥራ አስፈፃሚ: እንዲሁም የጸጥታ አካላት የፈተና ግብረ ሀይል ኮሚቴ አባላት ሆነው እየተሰራ እንደሆነ ተገልጿል።
================
ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ
ማህበረሰቡን እናገለግላለን !!!
✍🏾ይስፋዘር ከበደ
📝መድ አድ አበጋር
የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ትክክለኛ የማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይከተሉ::
ፌስቡክ👇
ዌብሳይት👇
ትዊተር👇
ቲክቶክ👇

Leave a Reply

Your email address will not be published.