‹‹ማህበረሰቡን እናገለግላለን››

‹‹ማህበረሰቡን እናገለግላለን››

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም ያሳተመው

‹‹ማህበረሰቡን እናገለግላለን››

የሚል መሪ ቃል ያለው የሠመራ ዩኒቨርሲቲ ሦስት የልዕቀት ማዕከላት አሉት። 

አርብቶ አደር ግብርና፣ የሥነ ምድር ሳይንስ እና ቱሪዝም ናቸው። ዩኒቨርሲቲው ቱሪዝምን እንደ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የልዕቀት ማዕከል አድርጎ የያዘ ሲሆን ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን የአፋር ክልል የሚታወቅባቸውን የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መስሕቦች ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ እንዲሆኑ፣ በዚህም ሕብረተሰቡ ተጠቃሚ እንዲሆን ይሰራል። ማዕከሉ የባህላዊ ተውኔቶችና ቴአትር ክፍሎችን ጨምሮ በርካታ ክፍሎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህ ክፍሎች ሰፊ የሚባለው የሚዳሰሱ ቅርሶች የሚገኙበት ክፍል ነው። በዚህ ክፍል ውስጥ ከጎረቤት አገራት ኤርትራ እና ጅቡቲ፣ እንዲሁም ከግብጽና ቱርክ የአፋር ታሪክና ቅርስ የሆኑ ቅርሶች ተሰብስበው የሚገኙበት ነው። እነዚህም የባህል አልባሳት፣ ከእንጨት፣ ከቆዳ እና ከብረት የተሰሩ ባህላዊ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ ባህላዊ የመዋቢያ ቁሶች፣ ባህላዊ የጦር መሳሪያዎች የመሳሰሉት ናቸው።

ዩኒቨርሲቲው የባህል ምርምር ማዕከሉን ከማስገንባትም በተጨማሪ በቱሪዝም ልዕቀት ላይ ከአፋር ክልል ባህልና ቱሪዝም፣ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት እና ከብሔራዊ ሙዚየም ጋር በመተባበር የቱሪዝም መድረኮችን በማዘጋጀት ይሰራል ተብሏል። ሬዶ የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች ማዕከል በተመረቀ ዕለት 12 መጻሕፍት ተመርቀው ለንባብ ቀርበዋል። መጻሕፍቱ በአፋር ታሪክ፣ ባህልና ባለውለታ ሰዎች ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። መጻሕፍቱ የተጻፉት ለጊዜው በአፋርኛ እና ጥቂቶች ደግሞ በአረብኛ ቋንቋዎች ሲሆን በቀጣይ በሌሎች ቋንቋዎች ይተረጎማሉ ተብሏል። እያንዳንዱ የአፋር ባህል የየራሱ መጽሐፍ ይወጣዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፤ ለዚያውም በአንድ መጽሐፍ 

መግለጽ ከተቻለ ነው። ታሪክ እና ባህሎቻችን በዓመት ወይም በወራት አንድ ጊዜ በሚዘጋጁ መድረኮች ሊገለጹና ሊታዩ ስለማይችሉ በመጽሐፍ መልክ ማዘጋጀቱ የተሻለ ያደርገዋል። ጸሐፊዎቹ የአካባቢውን ቋንቋ፣ ባህልና ስነ ልቦና ስለሚያውቁት ተገቢ ማብራሪያ ያደርገዋል። ጊዜ 

ወስደው፣ አጥንተው ስለሚጽፉት ‹‹ይህን ያህል ደቂቃ  አለህ›› ተብሎ መድረክ ላይ ከሚያብራራ ሰው የተሻለ የመግለጽ አቅም ይኖራቸዋል። 

የአፋር ታሪክ፣ ባህልና ወግ የኢትዮጵያ መገለጫ ነው። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹ከዳሎል እስከ ዳሽን›› የሚባል ፕሮግራም አለ። የፕሮግራሙ ይዘት ሁልጊዜም ስለዳሎል እና ሰሜን ተራሮች ማውራት አይደለም። ሁለቱ ቦታዎች የተወሰዱት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ብዝሃነት ጥግ ለማሳየት ነው። ኢትዮጵያ በማህበረሰባዊ ባህል ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮም አስደናቂ ብዝሃነት ያላት ናት። በአንድ ወቅት፣ በአንድ ወር እና በአንድ ቀን ውስጥ እንደ ሰሜን ተራሮች ያለ በረዶ ያዘለ ብርድ እና እንደ ዳሎል ያለ እሳት የሚተፋ ሙቀት ያለባት አገር ናት። ይህን የአፋር ዳሎል ኢትዮጵያን ለመግለጽ እንጠቀመዋለን ማለት ነው።

በዳጉ ስም የተሰየሙ የመገናኛ ብዙኃን ፕሮግራሞች አሉ፤ የሚተነተንባቸው ስለአፋር ዳጉ ብቻ አይደለም። በዳጉ የተሰየመው መነሻ ስለሆነ እና የመታሰቢያነት ክብር ስለሚገባው ነው። ኢትዮጵያን ስንገልጽ የአፋርን ታሪክና ባህል መጠቀም በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ያስፈልገናል ማለት ነው። ስለዚህ ይህ የአፋር የባህልና አገር በቀል ዕውቀቶች የምርምር ማዕከል የኢትዮጵያ  ማዕከል ነው ማለት ይቻላል። ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም አገር በቀል ዕውቀቶችን እንዲህ ወደ ምርምር ሊያመጡ ይገባል! 

አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published.