SU Football Club

Camel Boys

ጊዜው የ2014 ዓ.ም መገባደጃ፣እንደ አለም በወረርሽኝ፣እንደ ሀገር በበሽታ፣ በጦርነት፣ በአንበጣ፣በጎርፍ፣ በመፈናቀል በመሳሰሉት ተደራራቢ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ፈተናዎች የተከሰቱበት ማግስት ነበር።

ጊዜ የወለደውን የችግር ቆፈን ሁሉ ሲታገል የቆየው ሰመራ ዩኒቨርሲቲ  የከረመበትን መቀዛቀዝተላቆ፣ተቋማዊ መነቃቃትን ለመፍጠር  መማር ማስተማሩን አስጀምሮ፣የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት እየከወነ ባለበት ወቅት፣በከፍተኛ አመራሩ በኩል  አንድ ሀሳብ ብልጭ አለ።

ይህ የሆነው በስፖርቱ ዘርፍ ክልሉን ለማነቃቃት እና ለወጣቶች መልካም እድልን ለማመቻቸት በማለም በቀድሞው ስሙ “የካዳባ አፋር እግር ኳስ ክለብ” ተብሎ የሚጠራውንና  በክልሉ  ስፖርት ቢሮ የሚተዳደረውን እግር ኳስ ቡድን የመረከብ  ሀሳብ ተጠነሰሰ።

ብዙም ሳይቆይ መስከረም 6/2015 ዓ.ም የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአፋር ክልል እግር ኳስ ጽ/ቤት አመራሮች እና የአፋር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ  ሀላፊዎች እንድሁም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት ክለቡ በዩኒቨርሲቲው ታቅፎ የስም ዝውውር ተደርጎለት “ሰመራ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ” ተብሎ እንድጠራ ተወሰነ።

ይፋዊ ስምምነቱ  በዩኒቨርሲቲው  የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አብዱራህማን ከድር እና የ”ካዳባ አፋር እግር ኳስ ክለብ” ተወካይ አቶ አሊሚራህ መሀመድ አማካኝነት ተደረገ።

ክለቡ በ2010 ዓ.ም  ጀምሮ በኢትዮጵያ ሊግ አንድ ውስጥ የአፋር ክልል ብቸኛው ተወካይ በመሆን ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን፣ዩኒቨርሲቲው ከተረከበው በኋላ በአዲስ መልክ ተደራጂቶ “የሰመራ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ” ሆኖ በያዝነው አመት በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ በምድብ “መ”  ውስጥ  መጫወት ጀመረ።

ክለቡ በአሁኑ ሰአት ሁለተኛውን ዙር ጨዋታ በቢሾፍቱ ከተማ እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ፣ በሊጉ 20 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ6 ጨዋታዎች ድል ሲቀናው፣ በ8 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርቶ፣ በ6 ጨዋታዎች ነጥብ ጥሎ፣ በአጠቃላይ በ26 ነጥብ፣ በሊጉ 6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የቻለ ሲሆን፣ገና  2 ቀሪ ጨዋታዎች ይቀሩታል።

የሰመራ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ  በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ “ምድብ መ” ሚያዚያ 2 ቀን ከጠዋቱ 3 ሰአት ላይ ደጋን ከተማን  በቢሾፍቱ ስታድዬም ገጥሞ 6 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ቡድኑ በተጋጣሚው ደጋን ከተማ ላይ ግማሽ ደርዘን ጎል በማስቆጠር ለ3 ተከታታይ ጊዜ የሆነውን ዲሉን አስመዝግቧል። በጨዋታው #አወል አብደላ 3 ጎሎችን በማስቆጠር  ሀትሪክ ሲሰራ #አብ ኢሴ 2 ግቦችን እና #ያሲን ጣሂር 1 ጎል ያሲን ጣሂር 1 ጎል አስቆጥሮ በድምሩ 6 ጎሎችን በማስቆጠር ክለቡን አሸናፊ አድርገውታል።

የዛሬውን ውጤት ተከትሎ ክለቡ ከነበረበት ሰባተኛ ደረጃ በአንድ በማሻሻል በምድቡ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ሰመራ ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ክለብ ከተመሰረተ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሊጉ ጥሩ ተፎካካሪ መሆኑን ማሳየት መቻሉ በክልሉ ብቃት ያላቸው እና ክልሉንም ሆነ ሀገርን ሊወክሉ የሚችሉ ወጣት ስፖርተኞች እንዳሉት ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል::

ለዚህም የዩኒቨርሲቲው አመራሮች በሳል አመራር እና ትኩረት የታየበት፣የዩኒቨርሲቲው ስፖርት ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህራን ቡድኑን በቅርበት በማስተዳደር፣በዋና እና ምክትል አሰልጣኝነት፣በቴክኒክ አሰልጣኝነት እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ፣እንዲሁም የተጫዋቾቹ የአካል፣የስነ–ልቦና ጥንካሬ እና የቡድን መንፈስ፣ በጋራ የፈጠሩት መስተጋብር ነው።

በቀጣይ ክለቡ እራሱን ችሎ የተሻለ እና ተፎካካሪ ሆኖ እንዲወጣ ከሚመለከታቸው የክልሉ አመራሮች ጋር በመተባበር ልዩ ልዩ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞችን በመቅረፅ ወደ ሥራ መግባት የሚጠበቅ ሲሆን፣ ክለቡ ለሌሎች ክለቦችና ፕሮጄክቶች መፈጠር አስተዋፅዖ እንዲያበረክት እና የተዳከመውን ስፖርታዊ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ ለማድረግ ክለቡን መደገፍ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት  ይጠበቃል።

ከወዲሁ ዲል እና እድልን ተመኘን