
ዩኒቨርሲቲው በፊልም ፣ ድራማ እና ቲያትር ፕሮዳክሽን ላይ ለተሰማሩ የአካባቢው ወጣቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና ሰጠ::
#ሰመራ_ዩኒቨርሲቲ_የካቲት26/2017
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በሰመራ ከተማ ለሚገኙ የ’ኢምቢዳ’ እና ‘ማላሳይ’ ፊልም፣ ድራማ እና ቲያትር ፕሮዳክሽን ማህበራት ወጣቶች የአቅም ግንባታ ስልጠና በተሳካ ሁኔታ ሰጥቷል።

ስልጠናው የተለያዩ የፊልም እና የቲያትር ፕሮዳክሽን ዋና ዋና ጉዳዮችን ያካተተ ሲሆን ከነዚህም መካከል የድርሰት አፃፃፍ ፣ የገፀ ባህሪ አመራረጥ፣ የመድረክ ዝግጅት፣ የካሜራ አጠቃቀም፣ የፎቶ እና የቪዲዮ ቀረጻ፣ በኮምፒውተር መተግበሪያ የድምፅ እና የምስል ቅንብር፣ ጥልቅ ንባብ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጠራ እንዲሁም በፕሮዳክሽን እና ስርጭት ስነምግባር ላይ ያተኮረ ነው::

በዶ/ር ሬዶ የባህል እና ሀገር በቀል ጥናቶች ማዕከል አማካኝነት የተዘጋጀው ይህ ስልጠና ፣ የድርሰት ፣ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ፣ የባህል ፣ የቋንቋና ስነ-ጽሁፍ ባለሙያዎች በትብብር ቀርቧል።
ለስድስት ቀናት የተሰጠው ይህ ስልጠና የንድፈ ሀሳብ እና የተግባር ስራዎችን ያካተተ ሲሆን: 39 የማላሳይ እና የኢምቢዳ ቡድን አባላት የሆኑ ወጣት የጥበብ ባለሙያዎችን ተጠቃሚ አድርጓል።
ሰልጣኞቹ በመርሃግብሩ ማጠቃለያ ወቅት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ በማህበረሰብ ግንዛቤ ላይ ያተኮሩ ሶስት የመድረክ ተውኔቶችን በማዘጋጀት ክህሎታቸውን አሳይተዋል።

መሀመድ አህመድ አበጋር
ያሬድ አለሙ
