
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ህክምና አገልግሎት መስጠት ጀመሩ።
ጎረቤታሞቹ ሠመራ እና ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ በአፋር እና አማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ተንቀሳቃሽ የእንስሳት ህክምናና የቅድመ መከላከል ክትባት (mobile Veterinary Service) አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል።

የአገልግሎቱ አላማ፣ በአዋሳኝ የዞን እና የወረዳ አካባቢዎች በርካታ የእንስሳት ሀብት የሚገኝበት፣ እንስሳቱ በገበያ፣ በግጦሽ እና ውሃ ለመጠጣት ዘወትር የሚገናኙበት በመሆኑ ለተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭነቱ፣ በተቋማቱ የጋራ ጥናት ተለይቶ፣ የቅድመ መከላከል ክትባት እና የጠቅላላ ህክምና አገልግሎት መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ነው ተብሏል::
በጭፍራ ወረዳ እየተሰጠ ባለው በአሁኑ የህክምናና ክትባት ዘመቻው ላይ ከሁለቱም ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ መምህራን እና ተማሪዎች እየተሳተፉ እንደሚገኝ ተገልጿል።

ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ በጋራ አገልግሎት በመስጠት ላይ የቆዩ ሲሆን፣ ይህንኑ ለማስቀጠል በህዳር 2018 ዓ.ም ድጋሜ የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ግንኙነታቸውን ማጠናከራቸው የሚታወስ ነው።