
Leading from the Middle ተቋምን ከመሀል ሆኖ መምራት ፕሮግራም ተጠናቀቀ።
ሰመራ_ዩኒቨርሲቲ_የካቲት_28/2018-የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መሀመድ ኡስማን ከ2015 አስጀምረው በየአመቱ የሚያካሂዱት “ተቋምን ከመሀል ሆኖ መምራት (Leading from the Middle)” ከተለመደው ከላይ ወደታች(Top to Down) የአመራር ስርዓት የተለየ የመምራት ዘይቤ ሲሆን፣ ተቋማዊ ልህቀትን ለማረጋገጥ ቁልፍ የሆኑ የስራ ክፍሎችን፣ ሰፊ ጊዜ ወስዶ የመስክ ምልከታ እና ከባለሙያዎች ጋር ውይይት የማድረግ እና ችግሮችን የመፍታት አቀራረብ እንደሆነ ይገለጻል::

የዘንድሮው “ተቋምን ከመሀል ሆኖ መምራት” ከየካቲት 24-28/2018 ድረስ በተለያዩ ሶስት የስራ ክፍሎች፣ ማለትም በመስክና የቤተ-ሙከራ አስተዳደር፣የስነ ምድር ትምህርት ቤት እና በቋንቋዎችና ኮሙኒኬሽን ኮሌጅ ሲካሄድ ቆይቶ ተጠናቋል::
የስነ-ምድር ትምህርት ቤት(School of Earth Sciences) የክልሉን የተፈጥሮ ፀጋዎች መሰረት በማድረግ አንዱ የዩኒቨርሲቲው የልህቀት ማዕከል ሆኖ በትኩረት እየተሰራበት ያለ በመሆኑ፣ ፕሬዚደንቱ እና ድጋፍ ሰጪ ቡድኑ ጥልቅ ምልከታ ያደረጉበት እና በትምህርት ቤቱ ስር ያሉ መምህራን እና ሰራተኞች ጋር ግምገማ ያደረጉበት መሆኑን ተመልክተናል::

በማጠቃለያ መርሃ-ግብር ቅኝት የተደረገበት የቋንቋዎችና ኮሙኒኬሽን ኮሌጅ ሲሆን፣ ይህ ኮሌጅ በዚህ አመት መጀመሪያ ላይ ከማህበራዊ እና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ተነጥሎ የወጣ፣ አራት ቋንቋዎችን እና አንድ የጆርናሊዝም ትምህርት ክፍልን ያቀፈ አድስ ኮሌጅ በመሆኑ፣ አመራሩን፣ ሰራተኞችን፣ የግብአትና የስራ ሂደቱን ያማከለ ምልከታ እና ውይይት ተደርጓል::
ኮሌጁ ዩኒቨርሲቲው የሚገኝበትን ስትራቴጅካዊ መገኛ ያገናዘበ፣ የክልሉን ቋንቋ አፋርኛን ጨምሮ የሀገር ውስጥ፣ ቀጠናዊና አለም አቀፋዊ ቋንቋዎችን አሁን ካለው የመደበኛ ትምህርት፣ በተጨማሪ የአጭር ጊዜ ስልጠና እንድሰጥ አቅጣጫ ያስቀመጠ ውይይት ተደርጓል::

አጠቃላይ የ Open Leadership ሂደቶቹን የፕሬደዳንት ፅ/ቤት የድጋፍ እና ክትትል ቡድን አስተባብሯል።