
ሁለቱ ዩኒቨርሲቲዎች በግመሎች ጤናና ደህንነት ላይ በትብብር የሚሰሩትን ፕሮጀክት አስጀመሩ::

ሠመራዩኒቨርሲቲህዝብግንታህሳስ_07/2018ዓም-አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሠመራ ዩኒቨርሲቲ፤ በ SPANA (ስፓና-ኢትዮጵያ) የሚደገፍ በግመሎች ጤናና ደህንነት (Camel Health and Welfare) ላይ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን የስምምነት ሰነድ ፊርማ እና የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም አካሂደዋል።
የፕሮጀክቱ አላማ የግመሎችን ጤናና ደህንነት ለመጠበቅ፣የህክምና፣የምርምር፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን ፣በተለይም ህብረተሰቡን፣ ተማሪዎችን ፣ ባለሙያዎችን እና ምሁራኑን ያሳተፈ ስራ በመስራት የግመሎችን ጤንነት እና ደህንነት የመጠበቅ ስራ መስራት ሲሆን፣ ለአምስት አመት እደሚቆይ እና ከ16 ሚሊየን ብር በላይ(ለ3 አመት) የሚተገበር በጀት እንደተያዘለት ተጠቁሟል::

ስምምነቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ተወካይ እና እንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጅ ዲን ዶ/ር ሂካ ዋቅቶሌ እና የሠመራ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተ/ም/ፕሬዚደንት አቶ አደም አሊ ፈርመውታል::
አፋር ክልል በኢትዮጵያ የግመል ሀብት ትልቁን ድርሻ የሚይዝ እና፣ ሠመራ ዩኒቨርሲቲም ግብርናን በትኩረት መስክነት ለይቶ የአርብቶ አደሩን ኑሮ የሚያሻሽሉ የተንቀሳቃሽ የእንስሳት ህክምና አገልግሎቶችን እየሰጠ ያለ በመሆኑ፣ ይህ ፕሮጀክት መምጣቱ የተሻለ ውጤት እና፣ ዘለቄታ ያለው ስራ ለመስራት የሚያስችል አቅም ይፈጥራል ሲሉ አቶ አደም አሊ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል::

በሀገራችን ከ20 ዓመታት በላይ በእንስሳት ደህንነት ላይ በመስራት ልምድ ያለው SPANA (እንግሊዝ ሀገር የሚገኝ ግብረ ሰናይ ድርጅት) እና ከ60 ዓመታት በላይ በዘርፉ ልምድ ያለው የአ.አ ዩኒቨርሲቲ ይህን ፕሮጀክት ለሀገር ወዳዱ የአፋር ህዝብ ይዘን በመምጣታችን ደስታ ይሰማናል ሲሉ ዶ/ር ሂካ ዋቅቶሌ ገልጸዋል::
በስምምነት ሰነድ ፊርማው እና የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንስሳት ህክምና እና ግብርና ኮሌጅ፣ የ SPANA እና የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፤ ዲኖች፤ ዳይሬክተሮች፤ባለሙያዎች እና መምህራን ተገኝተዋል::