
በአካባቢ ስሙ ‘አስኤራ’ ወይም ‘አስኤራይቶ (As-era/ As-erayto) በሳይንሳዊ ስሙ (Dracaena ombet) በመባል ይታወቃል::
በአካባቢ ስሙ ‘አስኤራ’ ወይም ‘አስኤራይቶ (As-era/ As-erayto) በሳይንሳዊ ስሙ (Dracaena ombet) በመባል ይታወቃል::
በአፋር ክልል ውስጥ ከሚገኙ በርካታ ሀገር በቀል ዛፎች ውስጥ አንዱ እንደሆነ ይነገራል:: በአሁኑ ሰአት የዚህ ዛፍ ዝርያ በመመናመን ላይ እንደሚገኝ ጥናቶች ይጠቁማሉ::
በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ህይወት ትምህርት ክፍል መምህር እና የሶስተኛ ዲግሪያቸውን በእፅዋት ሳይንስ ዘርፍ በመከታተል ላይ የሚገኙት መ/ር መሀመድ ሹምባህሪ ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው እናቀርባለን::
#ሠዩ:-በቅድሚያ ለዚህ ቃለ-መጠይቅ ፈቃደኛ ሆነው ሙያዊ ትንታኔ ለመስጠት ስለመጡ አመሰግናለሁ::

#መሀመድ:- እኔም አመሰግናለሁ::
#ሠዩ:- ባለፈው ሳምንት እርሶ ከሌሎች ተመራማሪዎች ጋር በጋራ የሰራችሁት የምርምር ስራ በፈረንጆች አቆጣጠር 16 April 2025 መታተሙን ተመልክቻለሁ። እስኪ ስለ እትሙ ትንሽ ይንገሩኝ?
#መሀመድ:-አስኤራን በተመለከተ በዋናነት ጥናት እየሰራሁ ያለሁ ቢሆንም ፣ ጥሩ የምርምር ውጤት እንዲሆን ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት publication ላይ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን በቀላሉ በማለፍ ይህ ምርምር ፣ Springer Nature በተባለ አለም አቀፍ ጆርናል ፣ የ Biodiversity and Conservation አምድ ላይ “Dracaena ombet in peril in Ethiopia: a call for attention and action” በሚል ርዕስ ማሳተም ችለናል። ለዚህም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በዚህ ጥናታዊ ፅሁፍ ላይ አብረውኝ በመስራት የተሳተፉትን ተመራማሪዎችን ሁሉንም አመሰግናቸዋለሁ።
#ሠዩ:- እስኪ ስለ አስኤራ ዛፍ ምንነት እና ጥቅሞቹን ይግለፁልኝ?
#መሀመድ:- የአስኤራ ዛፍ ድርቅን የመቋቋም ችሎታ ያለው ፣ ቅጠሉን እንስሳት ይመገቡታ ፣ ፍሬውን ደግሞ ሰዎች ለምግብነት እንደሚጠቀሙት እንዲሁም ለመድሀኒትነት ይውላል:: የአስኤራ ግንዱ ለቤት እቃዎች ማለትም ለወተት ማለቢያ ፣ ለአይብና ቅቤ መያዣ ፣ ለገንፎ ማቅረቢያ ፣ ለንብ ቀፎ መስሪያነት እንዲሁም በስሩ ከፀሀይ ተከልሎ አረፍ ለማለት የሚጠቅም አይነተኛ የደረቃማና የህፀተ-ዝናብ አካባቢ ዛፍ ነው::
#ሠዩ:- የአስኤራይቶ ዛፍ ከኢትዮጵያ ውጭ እና በሀገራችን እና የት የት አካባቢ ይገኛል ፣ በምን ሁኔታ?
#መሀመድ:- በአሁኑ ሰዓት አስኤራ ከኢትዮጵያ ውጪ በግብፅ ፣ ሱዳን እና የመን የሚገኝ ሲሆን ፣ እፅዋቱ በከፋ ደረጃ እየተመናመነ በመሆኑ IUCN በአለም አቀፍ ደረጃ አደጋ ላይ ያለ እፅዋት በሚል ተርታ አሰለፎት የሚገኝ የእፅዋት ዝርያ ነው።
አስኤራይቶ እስከ አሁን በተደረጉ ጥናቶች በኢትዮጵያ ውስጥ በአፋር ክልል ፣ በትግራይ ክልል አንዳንድ ቦታዎች እና በሶማሌ ክልል እንደሚገኝ አመላክተዋል። በተለያዩ የተፈጥሮና ሰው-ሰራሽ ምክንያቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥሩ በመመናመን ላይ የሚገኝ ተክል ነው።
#ሠዩ:- የሰራችሁት ጥናት አስኤራይቶን ለመታደግ ምን አስተዋጽዖ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?
#መሀመድ:- አሁን Springer Nature ላይ ታትሞ በወጣው ጥናት ላይ ከሠመራ ዩኒቨርሲቲ እኔን ጨምሮ የመቀሌ፣ የአድግራት ዩኒቨርሲቲዎች እና የፐኢለኢም ኢትዮጵያ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ነው:: በጥናቱ እፅዋቱ ያለበትን ደረጃ እና መታደግ የሚቻልባቸውን ምክረ ሀሳቦች ጭምር አስቀምጠናል:: ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ ጥናቶች በመቀሌ፣ በአዲስ አበባ፣ በአዲግራት እና በሠመራ ዩኒቨርሲቲዎች የተከናወኑ እና በመከናወን ያሉ ሳይንሳዊ ጥናቶች እፅዋቱን መታደግ አስፈላጊ እና ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን ይጠቁማሉ።
#ሠዩ:- አስኤራይቶንም ሆነ ሌሎች በመመናመን ላይ ያሉ ሀገር በቀል እፅዋቶች ለመታደግ እንደ ዩኒቨርሲቲ ምን እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው?
#መሀመድ:- ጥናቶችን መሠረት በማድረግ በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት ፅ/ቤት ስር የተቋቋመ የደረቃማ አካባቢ ብዝኃ-ህይወት ምርምር: ልማትና ጥበቃ ማዕከል ተቋቁሟል:: ይህም በተቋማችን ዋናው ግቢ ውስጥ ለሀገር በቀል ዛፎች ማዕከልነት የሚውል ቦታ በመረከብ ከክልሉ የተለያዩ ወረዳዎች የእፅዋት ዘር እና ቡቃያ በማሰባሰብ ቦታውን የማልማት ስራ ለመጀመር ዝግጅቱ ተጠናቋል:: ይህንንም ማዕከል እኔ በሀላፊነት እያስተባበርኩ እገኛለሁ።
በማእከሉ ለማልማት ከታቀዱ ሀገር በቀል ዛፎች ውስጥ አስኤራ ይገኝበታል። ማዕከሉ የመማር ማስተማር እና የምርምር ማዕከል ከመሆን ባሻገር ለአካባቢው ማህበረሰብ የተለያዩ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ይሆናል። በተጨማሪም ሀገር በቀል ዛፎችን ችግኝ በማፍላት ለህብረተሰቡ የማከፋፈል እቅድም ተይዟል:: በዚህ በኩል ሀሳቡን በመደገፍ ስራውን በማስቀጠል ከግብ ለማድረስ ላለው ተነሳሽነት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራር ምስጋና ይገባቸዋል::
#ሠዩ:- እጩ ዶ/ር መሀመድ ሹምባህሪ የአስኤራይቶ እፅዋትን አስመልክቶ ለሰጡን ሰፋ ያለ ሙያዊ ትንታኔ በሠመራ ዩኒቨርሲቲ ስም አመሰግናለሁ::
ውድ አንባቢያን በዛሬው ዘገባችን በሠመራ ዩኒቨርሲቲ የስነ-ህይወት ትምህርት ክፍል መምህር እና የሶስተኛ ዲግሪ በእፅዋት ሳይንስ ዘርፍ በመከታተል ላይ ከሚገኙት መ/ር መሀመድ ሹምባህሪ ጋር ያደረግነው ቆይታ ይህን ይመስል ነበር:: ይህን ፕሮግራም በማዘጋጀት ወደ እናንተ ያቀረብኩት እኔ #መሀመድ_አህመድ_አበጋር ከህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ ነው:: በሌላ ምንባብ እስከምንገናኝ ሰላም ለሁሉም!
N.B:-ይህ የአስኤራ ፎቶ የተነሳው በኢረብቲ-አብአላ መንገድ የአዱ ተራራ አካባቢ ነው።
