
የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ትምህርታዊ ጉብኝት አደረጉ::
#ሠመራ_ዩኒቨርሲቲ፣ሚያዚያ 09/2017-የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ትናንት እና ዛሬ ባዘጋጀው ትምህርታዊ ጉብኝት የሰመራ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የመግለኪቦ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ታዳጊ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ተገኝተው በዶ/ር ሬዶ የባህልና አገር በቀል ጥናቶች ማዕከል የሚገኙ የታሪክ : የባህል እና የቅርስ ስብስቦችን እንዲሁም ትልቁን ቤተመጻሕፍ ጎብኝተዋል።

የጉብኝቱ ዓላማ ተማሪዎች ለባህል ፣ ለታሪክ እና ለትምህርት ያላቸውን ግንዛቤ በማጎልበት ፣ ቀደምት አባቶች/እናቶች የሰሩትን የማድነቅ ባህል እንድኖራቸው እና እነሱ በተራቸው በትምህርታቸው ጠንክረው ሰርተው የማህበረሰቡን ኑሮ የሚያሻሽሉ ፈጠራዎችን ለመስራት ተነሳሽነትን እንዲኖራቸው ማድረግ ነው።
ጉብኝቱን የምርምርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ም/ፕሬዝዳንት አቶ አደም አሊ: የማህበራዊ ሳይንስ እና ስነሰብ ኮሌጅ ዲን አቶ ሀቢብ መሀመድ : በዶ/ር ሬዶ የባህል ማእከል አስጎብኝ መ/ር ሙሳ አብደላ መርተውታል።
አመራሮቹ ከጉብኝቱ በተጨማሪ የህይወት ክህሎት ትምህርቶችን አካፍለዋል:: የጉብኝት መርሃ ግብሩ በሌሎች ትምህርት ቤቶችም እንደሚቀጥል ተገልጿል።

መሀመድ አህመድ አበጋር
ያሬድ አለሙ