
ዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ፕሮግራሞች ያሰለጠናቸውን ከ1 ሺ በላይ ተማሪዎች አስመረቀ::
ሰመራ_ዩኒቨርሲቲ_መጋቢት_13_2018_ዓም-የሰመራ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች በመደበኛ እና በኤክስቴንሽን ፣ በእረፍት ቀናት መርሐ-ግብሮች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ ከ1 ሺ በላይ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት ለ17ኛ ጊዜ በድምቀት አስመርቋል።
የእንኳን ደስ አላችሁና ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መሀመድ ኡስማን ከ 9 መቶ 87 የመጀመሪያ ድግሪ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች ውስጥ 82% ያህሉ ብሄራዊ የመውጫ ፈተና በተሳካ ሁኔታ ማለፍ መቻላችሁ፣ ለእናንተም ሆነ ለዩኒቨርሲቲው የላቀ ስኬት ነው ብለዋልዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታችሁ ያገኛችሁትን እውቀት እና ክህሎት ማህበረሰቡን በቅንነት እንድታገለግሉበት ይጠበቅባችኋል ያሉት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ በየምትሄዱበት ሁሉ የዩኒቨርሲቲው እና የአፉር ህዝብ አምባሳደር በመሆን እንድታገለግሉ ሲሉም አሳስበዋል።

የዕለቱ የክብር እንግዳ፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር ዲኤታና የዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ፣ ክቡር አቶ ስለሽ ግርማ ለተመራቂዎች ባስተላለፉት መልእክት “የዛሬውን ምረቃ ልዩ የሚያደርገው፣ ዩኒቨርሲቲው 20ኛ አመት የምስረታ ታሪካዊ በዓሉን በመጪው አመት ለማክበር ዝግጅት በሚያደርግበት ወቅት ላይ በመሆኑ፣ የዛሬ ተመራቂዎች የነገ አልሙናዮች እና የታሪኩ አካል ናችሁ ሲሉ ገልጸዋል።


አቶ ስለሺ በተጨማሪም “አፋር በቱሪዝም ሀብት የበለጸገ ክልል ነው። እነዚህ ሀብቶች ገና ያልተነገረላችው ናቸው። በዚህ ዘርፍም ሆነ በሌላ መስክ የተመረቃችሁ፣ ሁላችሁም የሀገራችን የወደፊት ዕድገት ባለድርሻ መሆናችሁን አውቃችሁ፣ እውቀታችሁንና ጊዜያችሁን ሀብቶቿን፣ በማስተዋወቅ፣ በማልማት እና በማስተዳደር ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ” ብለዋል።



