
የትምህርት ሚኒስቴር ሱፐርቪዥን ቡድን ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች (የማኔጅመንት አባላት) ጋር የማጠቃለያ ውይይት አደረገ።
#ሰመራ_ዩኒቨርሲቲ_ሚያዚያ/17/2017 ዓ/ም-በሰመራ ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ሚኒስቴር ሱፐርቪዥን ቡድን ለሁለት ቀናት ያደረገውን የውይይት እና የምልከታ መርሃግብር ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች (የማኔጅመንት አባላት) ጋር ባደረጉት የማጠቃለያ ውይይት እና ሪፖርት አጠናቀዋል።
በትናንትናው እለት ከተማሪዎች ፣ ከመምህራን፣ ከአስተዳደር ሰራተኞች እና ከመካከለኛ አመራሮች ጋር በተናጠል ባደረጉት ውይይት የወሰዷቸውን ነጥቦች ፣ዛሬ ካደረጉት የተለያዩ የመሰረተ ልማቶች እና የስራ ክፍሎች የመስክ ምልከታ የያዟቸውን ነጥቦች አንድ ላይ አጠቃለው ከከፍተኛ አመራሩ ጋር ተወያይተዋል።

በሁለቱ ቀናት ውይይቶች እና ምልከታዎች በተቋሙ እየተተገበሩ ያሉ የአስተዳደር ፣ የመማር ማስተማር ፣ የምርምር እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጉዳዮችን ከቁልፍ የአፈፃፀም አመልካቾች (KPI) አንፃር ጥንካሬዎችንና ክፍተቶችን በመለየት ገንቢ ውይይት አድርገዋል::
ልኡኩ በቆይታው በጥንካሬ የወሰዳቸውን አፈፃፀሞች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ: ማስተካከያ የሚፈልጉ ብሎ የለያቸውንና በዩኒቨርሲቲው ደረጃ መፈታት የሚችሉትን በትኩረት እንዲሰራባቸው: የትምህርት ሚኒስቴርን ድጋፍ የሚሹ ጉዳዮችን ለሚኒስቴር መስሪያቤቱ እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል::

በተለይም የመንግስትን ልዩ ትኩረትና ድጋፍ የሚፈልጉ የአካባቢው የሙቀት ሁኔታ ያገናዘበ የበጀት ድልድል እና የመብራት የሀይል አቅርቦት: የሀገር አቀፍ ፈተናዎች መርሃግብር እና ሌሎችንም ጥያቄዎች ለበላይ አካል እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል::
ዩኒቨርሲቲው ከተፈጥሮ ጋር እየታገለም ቢሆን አመራሩ በየደረጃው እና ሰራተኛው በመናበብ የሰሯቸው በርካታ ለሌሎችም ተሞክሮ የሚሆኑ አሰራሮችን እና ተቋማዊ ባህሎችን እንደተገነዘቡ ገልጸዋል::

በመጨረሻም የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር መሀመድ ኡስማን በልኡኩ እና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ መካከል ለተደረገው ነፃ ውይይት እና የመስክ ምልከታ መሳካት የዩኒቨርሲቲውን ማህበረሰብ እና ልኡኩን አመስግነው: ይህም ጥንካሬዎቻችንን በማስቀጠሉ ረገድ እና ክፍተቶቻችን ለይትን ለመሙላት : በተለይም የቁልፍ ተግባራትን ትኩረት ሰጥተን ለመፈጸም ያስችላል ብለዋል።